ONE LORD,ONE FAITH,ONE BAPTISM,

ONE GOD AND FATHER OF ALL,WHO IS ABOVE ALL,AND THROUGH ALL,AND IN YOU ALL. EPHESIANS.4:5-6

Wednesday, April 11, 2012

‹‹ሰሙነ ሕማማት››
‹‹ሰሙነ ሕማማት›› መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የምትጓዝ አካል አድርገው ሊገልጧት ይሞክራሉ፡፡ ይህ እጅግ አላዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኘና በሥጋዊና በደማዊ እውቀት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት የላትም፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ‹‹ከሕማማቱ በኋላ›› በማለት ስለ ሰሙነ ሕማማት የሚያወሳ ቃል ተጠቅሟል፡፡ (የሐዋ1፥3)
ሰሙነ ሕማማት የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፡፡ ‹‹ሰሙን›› የሚለው ቃል ‹‹ሰመነ›› ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ስምንት ቀኖች ወይም ሳምንት ማለት ነው፡፡ ‹‹ሕማማት›› የሚለው ቃልም እንደዚሁ ‹‹ሐመመ›› ወይም ‹‹መ›› ጠብቆ ሲነበብ ይጎረድና ‹‹ሐመ›› ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መከራዎች ማለት ነው፡፡ ይህ ለብዙ ሲሆን ነው፡፡ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ደግሞ ‹‹ሕማም›› እንላለን፡፡ እንግዲህ ሁለቱን ቃላት በማናበብ ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ስንል ‹‹የመከራዎች ሳምንት›› ማለታችን ነው፡፡
ሕማማት ስንል ምን ዓይነት ሕማም ወይም ምን ዓይነት መከራ በማን ላይ የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሰዎች ልዩ ልዩ አደጋ ሲደርስባቸው መከራ አገኛቸው ይባላል፡፡ በሽታ ሲይዛቸውና በደዌ ሲሰቃዩ መከራቸውን አዩ እንላለን፡፡ ያላቸውን ሲያጡና ኪሣራ ሲደርስባቸው ሌላው ቀርቶ ሲርባቸውና ሥራ ሲበዛባቸው እንኳን መከራቸውን አዩ ይባላል፡፡
በሰሙነ ሕማማት የምናስበው የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ከላይ ለሰው ልጆች ከጠቀስነውና ከተለመደው ዓይነት መከራ ይለያል፡፡ የተለየ ጊዜ ተወስኖለት ሰሙነ ሕማማት፣ ሕማማተ መስቀል፣ ሕማማተ ክርስቶስ ወዘተ እያልን በተለየ መንገድና ሥርዓት የምንገልጽውም ልዩ መከራ ስለሆነ ነው፡፡
ሕማማት የምንለው ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ አይሁድ የተቀበለው የሐሰት ክስ፣ ፍርድ፣ መጎተት፣ መገረፍ፣ መገፈፍ፣ እርግጫ፣ ጥፊ፣ ጡጫ፣ ችንካር በአጠቃላይ በበርካታ ድርሳናት የተገለጠው አይሁድ የፈጸሙበትን ግፍ ሁሉ ነው፡፡ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ በዓላማው፣ በአፈጻጸሙ፣ በመጠኑ፣ በምክንያቱ በአጠቃላይ በምን መልኩ ከሰው ልጆች መከራ ጋር አይመሳሰልም፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ ወልደ እግዚAብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡፡›› ይለዋል፡፡ (ኢሳ፶3፥3) ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ስለእኛ ሲል ነው፡፡ በእኛ ላይ መድረስ የነበረበትን መከራ ሁሉ እርሱ ተሸከመልን፡፡ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን፡፡ ይህን ሲያስረዳን ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ሕመማችንንም ተሸክሞአል፡፡›› በማለት ጻፈልን፡፡ (ኢሳ፶3፥4) ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው በፈቃዱ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ መከራን ተቀበለ ማለት ግን ግድሉኝ፣ ቸንክሩኝ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አይሁድ መከራ ሲያደርሱበት እነርሱን መቃወም፣ ማጥፋት፣ ወይም እንዳያገኙት ማድረግ ሲችል መከራን ተቀበለ ማለት ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እርሱ ባልሄደበት መንገድ በየዓመቱ የክርስቶስን ሕማማት ለማሰብ እያሉ ቸንክሩን፣ ግረፉን፣ ስቀሉን የሚሉ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ተፈጥረዋል፡፡ ይህም በገዛ ሐሳባቸው የሚመሩና ሥርዓት የሌላቸው መሆናቸውን ከማሳየት በቀር የሚጠቅማቸው ነገር የለም፡፡ ይልቅ በውስጡ ብዙ ኃጢአት፣ የእውቀት ማነሥ፣ ወንጀል የሞላበት አካሄድ ነው፡፡
እርሱ ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ እኛ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ማሰብ አያቅተንም፡፡ እንድናስበውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራውን እንድናስብለት ይፈልጋል፡፡ እርሱ ራሱ አማናዊ ሥጋውንና ደሙን
በሰጠን ጊዜ ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ብሎናልና፡፡ ሥጋውና ደሙ በመከራው ጊዜ የተሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ በሥጋውና በደሙ መከራውን እናስባለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋውን በበላችሁ ደሙን በጠጣችሁ ጊዜ እለት እለት ሞቱን ትናገራላችሁ›› ያለን ስለዚህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አክብራ በመያዝ ዘወትር በቅዳሴዋ ‹‹ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ - አቤቱ ሞትህን እንናገራለን፡፡›› ትላለች፡፡
የጌታችን የመከራው መታሰቢያ እንዲደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሆኑን ከላይ አብራርተናል፡፡ ያ ደግሞ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚደረግ አይደለም፡፡ ‹‹ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን›› (1ቆሮ04$፵) ስለተባለ ቤተ ክርስቲያን የጌታችችን ሕማማት የምታስብበት ልዩ ወቅትና ሥርዓት አላት፡፡ ወቅቱ በየዓመቱ ለአንድ ሳምንት ሲሆን ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› ይባላል፡፡ ሳምንቱ የሚታወቅበት ልዩ ሥራ ደግሞ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደትና መጻሐፍትን ማንበብ ሲሆን ይህም ‹‹ግብረ ሕማማት›› ይባላል፡፡ ይህን ሥርዓት ለማካሄድ የሚረዳው የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ እንደ ግብሩ ‹‹ግብረ ሕማማት›› ተብሏል፡፡
‹‹እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ወያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም፡፡›› አሜን!
በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
E-mail - hibretyes@yahoo.com

No comments:

Post a Comment