ONE LORD,ONE FAITH,ONE BAPTISM,

ONE GOD AND FATHER OF ALL,WHO IS ABOVE ALL,AND THROUGH ALL,AND IN YOU ALL. EPHESIANS.4:5-6

Thursday, May 24, 2012

ጾ መ ሐ ዋ ር ያ ት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን። ጾም ማለት ከምግብና ከመጠጥ ራስን በማቀብ በአንቃዕዶ ልቦና በሰቂለ ኅሊና ሆነን ወደ ፈጣሪ የምንቀርብበትና ለሰራነው ኃጥያት ይቅርታን ፣ለመጣብን ቁጣ ምህረትን፣ለደረሰብን ሕመም ፈውስን ከፈጣሪ ዘንድ የምናገኝበት የእምነት መገለጫ መንገድ ነው። ጾምን ያዘዘው እግዚአብሔር ሲሆን ስርአቱም የተሰራው በአዳምና በሔዋን ዘመን ነው።ከዛም በአበውና በነብያት ሲፈጸም የኖረና በራሱ በእግዚአብሔር ወልድ የጸና ሥርዐት ነው። አዳምና ሔዋን ገና በገነት ሳሉ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ብሉ ይህንን እንዳትበሉ ብሎ የሚበላና የማይበላውን ወይንም የሚጾመውንና የማይጾመውን ምን እንደሆነ አዟቸዋል።ዘፍ. ፪፥፲፯ “ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ። ’’ ይህን በእግዚአብሔር የተሠራ ሥርዓት በማፍረሳቸው አዳምና ሔዋን ተቀጥተዋል።ከገነት ተባረሩ በመጾም ይገኝ ከነበረው ጸጋና በረከት ተለዩ።ይህን ታሪክ የሚያውቁ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ወደተጠሩበት ወንጌልን ለዓለም የማዳረስ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት እግዚአብሔር መጀመሪያ ለሰው የሰጠውን ትእዛዝ ራሳቸው ፈጽመው ሌሎችም ይፈጽሙት ዘንድ ለማስተማርና አገልግሎታቸውም የሰመረ ይሆን ዘንድ አገልግሎታቸውን በጾም ጀምረዋል። ጾም ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩበት እግዚአብሔርን የሚያዩበት መሳሪያ ነው።ሊቀ ነብያት ቅዱስ ሙሴ በሲና ተራራ ከእግዚአብሔር ጋር የተነጋገረውና የአምላኩን ፊት ሊያይ የበቃው ፵ ቀንና ሌሊት ራሱን በጾም ወስኖ ነው። የእግዚአብሔር ማደሪያ የቃል ኪዳኑን ታቦትም ከእግዚአብሔር እጅ ለመቀበል በቃ።ዘዳ. ፱፥፱። የሐዲስ ኪዳን ደቀመዛሙርትም ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ጸጋና ኃይል ይሰጣቸው ይበዛላቸው ዘንድ በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ ቀርበዋል። “…እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።በዚያን ጊዜ ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።’’ ሐዋ.፲፫፥፪-፫ ። እኛም ይህን የበረከት ጾም ጾመን በረድኤት እንድንኖር አምላከ ሐዋርያት ይርዳን። አሜን!

Saturday, May 19, 2012

ቅዱስያ ያሬድ የደረሳቸው መጽሐፍት፦ - ፩. ድጓ፦ ድጓ የቤተክርስቲያን ዜማ መድብል ሲሆን ዐራት ክፍሎች አሉት እነዚህም በአራቱ የአመት ዘመናት/seasons/ ማለትም በመጸው፣በሃጋይ/በጋ/፣በፀደይና በክረምት ይመደባሉ። አራቱ ክፍሎችም፦ - ሀ - ድጓ ዮሐንስ፦ ስለቅዱስሐንስ መጥምቅ የሚናገር/የሚዘመር ነው። ከመስከረም ፩ እሰከ ኅዳር ፴ ድረስ የሚዘመሩ መዝሙራትን ይዟል። - ለ - ድጓ አስተምሕሮ፦ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት ያደረገውን ተአምራት የያዘ ነው። የሚዘመርበትም ወቅት ከታኅሣስ ፩ እስከ መጋቢት ፴ ባለው ወቅት ነው። - ሐ - ጾመ ድጓ፦ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን በተለይ በአብይ ጾም የሚዘመሩ መዝሙራትን የያዘ ነው። - መ- ድጓ ዘፋሲካ፦ ከትንሳኤ እሰከ ጷግሜን ባለው ጊዜ ውስጥ የሚዘመሩ መዝሙራትን ያካተተ ሲሆን ሰለ ጌታ የማዳን ሥራ፣ ስለእርገቱ፣ስለመንፈስ ቅዱስና ስለክረምት የሚያወሳ ነው። - ፪. ጾመ ድጓ፡- በአብይ ጾም የሚዘመሩ መዝሙራትን የያዘና ስምንት ክፍሎች ያሉት ነው። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው። - ሀ-ዘወረደ ለ-ቅድስት ሐ-ምኩራብ መ-መጻጉ ሠ-ደብረዘይት ረ-ገብርሔር ሰ-ኒቆዲሞስ ሸ-ሆሳዐና - ፫. ዝማሬ፦ በህብረት/በማህበር የሚደርስ ጸሎት/መዝሙር የያዘ ነው። ከቁርባን በኋላ የሚባል ነው። ዝማሬ በአምሰት ይከፈላል፦ ሀ-ህብስት ለ-ጽዋዕ ሐ-መንፈስ መ-ምስጢር ሠ-አኮቴት ይባላሉ - ፬. መዋስዕት፦ ስለጌታችን ጥምቀት፣ትንሳኤና እርገት፣ስለእመቤታችን አማላጅነት፣ስለቅዱሳን ክብርና አማላጅነት የሚዘሩ መዝሙራትን ያካተተ ነው። የሚዘመረውም ለሙታን መታሰቢያ፣ለሆሳዕና እና ለቅዳሜ ስዑር ነው። ቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ከተሰኘው ድርሰቱ ጋር የደረሰውና ከዝማሬ ጋር በአንድ ወንበር የሚሰጥ በመሆኑ ዝማሬ መስዋዕት በመባል ይታወቃል። - ፭. ምዕራፍ፦ የዜማ ስብሐተ ነግህ፣መወድስና ክስተት የተባሉትን የመዝሙር አይነቶች ያጠቃልላል። በተጨማሪም የዘወትር የዓመቱን ሳይጠብቅ በዓመት በበአላትና ሳምንታት የሚባል ነው። የዜማዎችን አይነትና ማረፊያዎች ከፋፍሎ የሚነግረን ክፍል ነው። በውስጡ የዜማ ተማሪዎች የሚማሯቸውን ትምህርቶች ይዟል። እነዚህም፦ ውዳሴ ማርያም፣ መስተጋብዕ፣አርባዕት መለኮት፣አርያም፣ክስተትና መወድስ ይባላሉ።